በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለልማት ምቹ ሁኔታ መኖሩን ባለሃብቶች ተናገሩ
ቡልቡላ፡- በኦሮሚያ ክልል ቡልቡላ የተገነባው የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና መሠረተ ልማቶቹ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸውን ባለሃብቶች ተናገሩ።
ትናንት የቡልቡላ ግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በፌደራልና በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ በስትሪንግ ኮሚቴ አባላት፣በቦርድ አባላት፣በአልሚ ባለሃብቶች፣በአጋር ድርጅቶችና በባለድርሻ አካላት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ተጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት ባለሃብቶች መካከል አቶ ምንተስኖት አእምሮ እንዳሉት፥ በፓርኩ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተስፋ ሰጪና ባለሃብቶችን የሚስቡ ናቸው። በተለይም በፓርኩ ውስጥ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች መሠረተ ልማቶች መሟላታቸው የባለሃብቱን ጥያቄ በከፍተኛ ደረጃ የሚመልስ ነው ብለዋል።
እንደ ባለሃብቱ ገለጻ፤ ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በቀላሉ ለማግኘት አመቺ ቦታ የተገነባ ከመሆኑም በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላ ስለመሆኑም ጠቁመዋል። ድርጅታቸውም በፓርኩ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ለማከናወን እንቅስቃሴዎችን መጀመሩንም አመልክተዋል።
ሌላኛው በጉብኝቱ ላይ የተገኙት ባለሃብት አቶ ቢንያም ባልቻ በበኩላቸው፤ በቡልቡላ ግብርናና ምርት ማቀነባበሪያ ፓርክ ውስጥ መሠረተ ልማቶች ከመሟላታቸው በተጨማሪ ባለሃብቶች በድርጅታቸው ስፍራ ሆኖ ለመከታተልና አመራር ለመስጠት ያመች ዘንድም በቅጥር ግቢው የመኖሪያ ቤት መገንባቱ እንዳስደነቃቸው አስረድተዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ በማር ማቀነባበር ላይ የተሠማሩት አቶ ቢኒያም ድርጅታቸው በቀን 5000 ኪሎ ግራም ማር እንደሚያመርትና ለዚህም አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።
ፓርኩ ውሃ፣ መብራትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ያሟላ ሲሆን በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ በመሆኑ የማር ምርቶቻቸውን ከኢትዮጵያ በዘለለ በአውሮፓና ሌሎች ሀገራት የገበያ መዳረሻ እያገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል። መንግሥትም ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ባለሃብቶችን የሚያነሳሳ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከዚህም በተጨማሪም የባለሃብቶችና መንግሥት የተናበበ አሠራር የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት በብዙ መንገድ በመደገፍ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።
በ1 ነጥብ2 ቢሊዮን ብር በፓርኩ ውስጥ ሁለት ሄክታር መሬት ተረክበው ግንባታ እያከናወኑ የሚገኙት አቶ ቶፊቅ ከድርም፥ በስድስት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ የሚያስገቡ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን አብራርተዋል።
የመሠረተ ልማት በሰፊው መሟላት፣ የክልሉ እና ፌደራል መንግሥት ልዩ ትኩረት መስጠት፣ አመቺ ስፍራ መኖሩንና ለማስፋፊያ የሚሆን ሰፊ መሬት መኖሩ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚመቻችበት ዕድል መፈጠሩና ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችም ባለሃብቶችን የሚስብና ለኢንቨስትመንት የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ ቱሳ እንዳሉት፥ ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ ሲሆን በአግሮ ፕሮሰሲንግ ተምሳሌት እንዲሆንም ጭምር የታሰበ ነው። ይህም በመሆኑ ለባለሃብቶች ጥሩ ዕድል የሚሰጥ ነው። የክልሉና የፌደራል መንግሥታት በተናበበ ሁኔታ መሠረተ ልማቶችን ማሟላታቸውንም አስረድተዋል።
ምንም እንኳን የቡልቡላ ግብርናና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዚህ ደረጃ የተገነባና ትኩረት የተሰጠው ቢሆንም አሁንም ቢሆን በርካታ ባለሃብቶችን እየተጠባበቀ መሆኑን አብራርተዋል። በመሆኑም ባለሃብቶች ዕድሉን እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
ከቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፥ ግንባታው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ባለሃብቶች በቅርበት ሆነው ሥራቸውን እንዲመሩና እንዲከታተሉ ከ240 በላይ መኖሪያ ቤቶች በውስጡ ተገንብተዋል። ቀደም ሲል በፓርኩ የውሃ ችግር የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አምስት ግዙፍ የውሃ ማከማቻ ታንከሮች መዘጋጀታቸውንና ለአገልግሎት መብቃታቸውም ተገልጿል።
በቡልቡላ ኢንቨስት አድርጉ
Hello, welcome to Bulbula Integrated Agro Industrial Park, we are the first choice for Asian, European and American foreign investors to invest in Bulbula IAIP…