የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገመገመ

የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገመገመ

የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሐምሌ 11/2014 ዓ.ም በዳንግላ ከተማ ገምግሟል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የእቅድ ዝግጅት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በልስቲ ወርቁ በበጀት ዓመቱ በቅድመ ዝግጅትና በተግባር ምዕራፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትና የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዲሁም ከመልካም አስተዳደር አኳያ ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሄዎችን በዝርዝር አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱም በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከግንባታ አኳያ የማጠቃለያ ስራ የሚፈልጉ አንዳንድ ስራዎች በትኩረት ተለይተው ፈጥነው ሊጠናቀቁ እንደሚገባና በግንባታ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችና መልካም ልምዶች ተቀምረው በቀጣይ በሰሜን ምዕራብ አማራ ለምንገነባው ፓርክ ጥቅም ላይ እንዲውሉ፣ በፓርኩ ውስጥ እየገቡ ለሚገኙ ባለሃብቶች የክትትልና ድጋፍ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ፣ ሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን በበጀት ታግዘው ሊለሙ እንደሚገባና በውሉ መሰረት ያለማ መሬት በሚነጠቅበት ጊዜ ባለድርሻ አካላት ተናበው ሊሰሩ ይገባል፣ ከገበያ ትስስርና ፕሮሞሽን ስራዎቻችን አኳያ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ቅንጅታዊና የተጠናከረ ስራ መስራት ይገባል፣ የቡሬ ፓርክና ገጠር ሽግግር ማዕከላትን የሀይል አቅርቦት ችግሮች በአጭር ጊዜ ለመፍታት ተከታታይ ጥረት ቢደረግ የሚሉና ሌሎች ሃሳቦች በተሳታፊው ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ጣምአለው እንደገለፁት ክልሉ በጦርነቱ ምክንያት የገጠመውን ቀውስ ለመመከት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ልማቱን ለማስቀጠል ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ተልዕኮውን ለማሳካት የሄደበት ርቀት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ከቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና ከ7ቱ የገጠር ሽግግር ማዕከላት ልማት አካያ የማጠቃለያ ስራ የሚጠይቁ ተግባራትን በመለየት ፈጥኖ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በሌላ በኩል ዋና ስራ አስፈጻሚው በሰሜን ምዕራብ አማራ የሚገነባውን አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጅምሩ ጀምሮ ስኬታማ ለማድረግ ያለቀለት የዲዛይን ስራ ጨምሮ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባና በ2015 በጀት ዓመት የኮርፖሬሽኑን ተልዕኮ ሊያሳኩ የሚችሉ ዋና ዋና ተግባራትን ለይቶ ማቀድና ውስጣዊና ውጫዊ ቅንጅታዊ አሰራር ስርዓታችን በማጠናከር ለእቅዶቻችን ስኬት ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡